ለዛሬ በአንድ ግለሰብ ላይ በዝግ ብሎግ እንድናወራ አነሆ ልጀምር ነው። (በነገራችን ላይ ዝግ ብሎግ ያልኩት እንደወትሮው ብሎጌ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ስለመታገዱ ላወራ አይይደለም። (በሌላ ቅንፍ ለድርጅታችን ከጠቀመ ልሳናችንም ቢዘጋ ቅር የማይለን ቁርጠኞች መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እወዳለሁ!) ይልቅስ በርዕሱ “ለኢህአዴግ አባላቶች ብቻ” ብዬ በማለቴ ሌሎች፤ ፅንፈኞች፣ አክራሪዎች፣ ነፍጠኞች፣ ነውጠኞች፣ ሽብርተኞች፣ ኒዬ ሊበራሎች፣ የሻቢያ ተላላኪዎች (ዉዉዉ ይሄንን ሁሉ ስም አውጥተንላቸዋል እንዴ ለካ…? ለነገሩ ከዚህም እጥፍ እጥፍ ስም አውጥተንላቸዋል። ለካስ ከኢኮኖሚ እድገቱ እኩል ተቃራኒዎቻችንን በመሞለጭም ታላቅ እምርታ አስመዝግበናልና! በእውኑ በድርጅቴ ኮራሁ! የሆነው ሆኖ፤ ባጠቃላይ እነዚህ ወዘተዎች ስለማያነቡት እና ጨዋታው የቤተሰብ ጨዋታ በመሆኑ ነው በዝግ ብሎግ ማለቴ!)))
http://www.youtube.com/watch?v=p7xtAH2aHA0&feature=youtu.be
እንደሚከተለው እጀምራለሁ…!
እኔ የምለው ባለፈው ግዜ ሰለ ጓድ ሰለሞን ተካ አንዳንድ ነገሮችን አንስቼ ተናግሬ ነበር። በርግጥ ግለሰቡ የተናገርኩትን ቢሰማም ቅሉ ሂሱን አልዋጠም። ሰሞኑን እንዳሰማሁት ደግሞ እንኳን ሂሱን እና መድሃኒቱንም በአግባቡ መዋጥ እንዳቆመ ያመላከተኝ ነገር አስተውያለሁ።
ተጠቃሹ ግለሰብ በግል ስሜቱ በመነሳሳት ፅናት በተባለ ራዲዮ ጣቢያው ላይ ድርጅታችንን ለዝቅጠት የሚዳርግ አንዳች ንግግር ተናግሯል። ሰሞኑን ጋዜጠኛ አበበ ገላው ስመ ገናናውን ጠቅላይ ሚኒስትራችን አምባገነን ብሎ በተናገረበት ንግግሩ ላይ ጓድ ሰለሞን ተካ ምላሽ ለመስጠት ሞክሮ ነበር። በእውነቱ ሙከራውን ሳላንደንቅ አናልፈም።
ነገር ግን፤
1ኛ ጉድ ሰለሞን ተካ (ይቅርታ ጓድ በሚል ይስተካከል) በራዲዮ ጣቢያው ላይ በንባቡ አንድ ታዋቂ ጋዜጠኛን ለማስመሰል በግልፅ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። በተጨማሪም ተደጋጋሚ የንባብ ችግር ይታይበት ነበር። እንደውም ይህንን የሰማ አንድ ለድርጅታችን ቅርብ የሆነ ግለሰብ ይህ ሰው ራዲዮ ጣቢያ ሳይሆን ፖሊስ ጣቢያ ነበር የሚገባው” ብሎ አስተያየት ሰጥቷል። (ፖሊስ ጣቢያ ይገባዋል ያለው እንዲታሰር ፈልጎ መሆኑ የገባኝ በስተ መጨረሻ ነው።) በማስመሰል ጥረቱ እና በንባብ ድንቅፋቱ የራዲዬ ጣቢያውን ሚኒ ሚዲያ አስመስሎታል።
2ኛ አባሉ በአሁኑ ሰዓት በራዲዮ ጣቢያው እያስተላለፈ ያለው አበል የተቀበለበትን የድርጅት ስራ ሳይሆን የተጣሉትን ግለሰቦች ለማብሸቀያ እንደሆነ ፍንጭ አግኝቻለሁ። በዚህም የተነሳ ድርጅታችን ላይ ተደጋጋሚ ነጥብ ሲያስቆጥርባት ይስተዋላል።
3ኛ ጓድ ሰለሞን ራሱም ሳያውቀው “በህቡዕ” ለሌላ ድርጅት እየሰራ እንደሆነ ለማየት ችያለሁ። እንዲህ የምለው ከመሬት ተነስቼ አይደለም። ነገር ግን የሚናገራቸው እጅግ ርካሽ የሆኑ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ስድባ ስድቦች ድርጅታችንን የሚያዋርዱ ከመሆናቸውም በላይ በተቃራኒው ደግሞ ለተቃዋሚዎች ትልቅ ግብአት እንደሚሆኑ በተግባር በመመልከቴ ነው።
4ኛ የዚህ አባል ጉዳይ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። የራዲዮ ፕሮግራሙ እንደማንኛውም ስልጠና እንደወሰደ ግለሰብ ተቃዋሚዎችን “የደርግ ርዝራዦች፣ ነፍጠኞች ሽብርተኞች…” ሲል መሳደቡ ጥሩ ሆኖ ሳለ በፕሮግራሙ መጨረሻ ላይ ግን “ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቆራጥ አመራር ጋር ወደፊት!” በማለት የቀድሞ የደርግ አባላት ለኮሎኔር መንግስቱ የሚያሙትን ፉከራ ስም ብቻ ቀይሮ አሰምቷል። በእውኑ ይሄ በድርጅታችን ላይ ታላቅ የመበስበስ አደጋ አይደለምን…?
100ኛ ባጠቃላይ ግለሰቡ ከላይ አንድ ወዳጄ ብሎኛል እንዳልኩት ራዲዮ ጣቢያ ሳይሆን ፖሊስ ጣቢያ የሚገባው ቢሆንም ድርጅታችን የምትታገስ ናትና ለጊዜው በትዕግስ እንድታለፈው አስተያየቴን ስሰጥ ቀጥሎ የሚገኘው የውሳኔ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆንበት አበክሬ እጠይቃለሁ።
የውሳኔ ሃሳብ
ይህ ግለሰብ ለኢህአዴግ እየሰራለት ነው ብዬ አላምንም። ከሆነም ደግሞ “ቆይ ባልሰራላችሁ!” በሚል ጥላቻ እና ቂም በቀል ኢህአዴግን ሊያጠፋ ቆርጦ የተነሳ ነው። (እርግጥ ነው ለተቃዋሚዎችም እየሰራ እንዳለሆነ ግልፅ ነው እናስ…? የተባለ እንደሆነ በግሉ ከወዲያ ማዶ ላለበት ብሽሽቅ ኢህአዴግን መጠቀሚያ ያደረገ ግለሰብ ነው። ይህም ግልፅ የሆነ ኪራይ ሰብሰቢነት እንደሆነ በተደጋጋሚ በተሰጡ ድርጅታዊ ስልጠናዎች ላይ ተረድተናል።) ስለሆነም በእውኑ ድርጅታችንን ከተጋረጡባት ሰርጎ ገቦች እና ጥቅመኞች የማዳን ጊዜው አሁን ነው። ከልባችሁ ለእናት ድርጅታችን ፍቅር ያላችሁ አባላት ዛሬውኑ ሰለሞን ተካ በኢህአዴግ ጉዳይ ላይ ትንፍሽ እንዳይል ድርጅታዊ ውሳኔ ይተላለፍ ዘንድ በተሰዉ ሰማህታት ስም እጠይቃለሁ። የግድ በአባልነት መቀጠል ካለበት ሰላማዊ ሰልፎች በሚኖሩ ግዜ መፈክሮችን ከተሸከመልን ይበቃል።
ከልማታዊ ሰላምታ ጋር!
No comments:
Post a Comment