አርቲስቷ ለጋዜጣው እንደገለጸችው፣ በቤቱ መቃጠል እጅግ አስፈላጊዋ የነበሩ ንብረቶችና መተኪያ የሌላቸው ሰነዶች ወድመውባታል፡፡ ‹‹እንኳን የሰው ሕይወት አልጠፋ፤›› በማለት መናገሯንም ሪፖርተር ጨምሮ ዘግቧል፡፡
ለኮርፖሬሽኑ ከሁለት ወራት በላይ ደጋግማ ብታመለክትም ምንም መፍትሔ ማጣቷን ለጋዜጣው የገለጸችው አርቲስቷ፣ ቤቱ በራሱ ጊዜ በመጋል የቧንቧ ውኃ ሳይቀር እያፈላ ሲያስቸግራት ቆይቶ ድንገት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሊነድ መቻሉን አስታውሳ፣ ቤቱ በእሳት መያያዙ የማያስገርምና ቀድሞም ቢሆን መቃጠሉ እንደማይቀር በስጋት ይጠበቅ እንደነበር ለጋዜጣው ገልጻለች፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከደንበኞቹ የሚፈልገውን እንደሚያገኘው ሁሉ በምላሹ ደንበኞቹን ለመርዳት አለመቻሉና ለአደጋ መንስዔ የሆኑ አጋጣሚዎችን እንዲያስተካክል ጥሪ ሲደረግለት ዝምታን መምረጡ እንዳሳዘናት ተናግራለች፡፡
በ500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ቪላ በእሳት ሲያያዝ ጎረቤቶችና የአካባቢ ሰዎች ከእሳት አደጋ መከላከያ ድርጅት ጋር በመሆን ሊያጠፉት ሞክረዋል፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት የተነሳውን ቃጠሎ ከመስመር አለያይተው ለማጥፋት የሞከሩት የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሠራተኞች፣ የኤሌክትሪክ መስመሩን ቆርጠናል ባሉበት አፍታ ከባድ እሳት መልሶ መንበልበሉ እንዳደናገጣቸው በመግለጽ ክስተቱን ታስታውሳለች፡፡ በዚህም ሳቢያ ቪላው ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጪ ሊሆን ችሏል ብላለች፡፡
በአርቲስቷ ቤት ላይ የደረሰውን ቃጠሎ በሚመለከት ሪፖርተር ጋዜጣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽን አነጋግሯል፤ ‹‹ቃጠሎ መድረሱን የሰማነው ቆይቶ ነው፡፡ አደጋው የደረሰው በኮርፖሬሽኑ ስህተት መሆን አለመሆኑን በማጣራት ላይ ነን፡፡ አርቲስቷ ቃጠሎ በደረሰ በ24 ሰዓታት ውስጥ አመልክታ ከሆነና ችግሩ የተከሰተው በኮርፖሬሽኑ ስህተት መሆኑ ከተረጋገጠ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ካሳ ይከፈላታል፤›› ማለታቸውን ሪፖርተር ጨምሮ ዘግቧል፡፡
No comments:
Post a Comment